ሐዋሳ ቅርንጫፍ
የቅርንጫፉ አባሎች ብዛት በፆታ
ፆታ | 2009 |
---|---|
የሴቶች | |
የወንዶች | |
ጠቅላላ አባሎች | 170 |
ሐዋሳ የደቡብ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ዋና ከተማ ናት። ከተማዋ በሐዋሳ ሐይቅ ዳርቻ የምትገኝ በጣም ማራኪ ከተማ ናት። ሐዋሳ ሐይቅ ደግሞ የብዙ የተለያዩ አእዋፍ መናኸርያ ናት።
በዚህች ውብ ከተማ ውስጥ የሚገኘው የኢመየብማ ቅርንጫፍ ንቁ ቅርንጫፍ ነው። የክልሉ የሠራተኛና የማኅበራዊ ጉዳይ ኤጀንሲ ድጋፍና ትብብር እንዲያደርግለት በመጠየቅ ከተማው አልፎ በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች ለሚገኙ መስማት የተሳናቸውም አገልግሎት ሲሰጥ ቆትቷል። በክልሉ ውስጥ ለሚገኙት የኢመየብማ ቅርንጫፎች መሪዎች የተለያዩ ሥልጠናዎች እንዲካሄዱ አድርጓል።
በ2006 ዓ.ም. ከኃይሌ ሪዞርት ባገኘው ትብብር ዓለም አቀፍ የመስማት የተሳናቸው ሳምንት አክብሯል። በዚህ አከባበር ሥነ-ሥርዓት ላይ ወደ 53 የሚሆኑ መስማት የተሳናቸውና ሌሎች እንግዶች የተሳተፉ ሲሆኑ፣ ኃይሌ ሪዞርት የስብሰባ አዳራሹን በነፃ ቅርንጫፉ እንዲጠቀምበት ከመፍቀዱም በላይ በተጨማሪም ለተሳታፊዎች ሻይ እና ቡና አቅርቧል።
በ2007 ዓ.ም. ከአለታ ዎንዶ ቅርንጫፍ ጋር በመተባበር ዓለም አቀፍ የመስማት የተሳናቸው ሳምንት አለታ ዎንዶ ከተማ ውስጥ ስብሰባ በማድረግ ታስቧል። በስብሰባው ላይ ከሐዋሳ የተጓዙ 35 መስማት የተሳናቸው አባሎች የተሳተፉ ሲሆኑ ከአለታ ዎንዶ ደግሞ 45 ተሳታፊዎች ተገኝተዋል። ከሐዋሳ ወደ አለታ ዎንዶ ለሄዱት መስማት የተሳናቸው አባሎች የክልሉ መስተዳድር ከነሾፈሩና ነዳጅ በለገሰው አውቶቡስ ደርሶ መልስ የተጓጓዙ ሲሆኑ፣ ብርሃን ለሕፃናት የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ በጎ አድራጎት ድርጅት ደግሞ ለቅርንጫፉ የብር 5,000 (አምስት ሺ ብር) ድጋፍ በማድረጉ ሥነ-ሥርዓቱ በተሳካ ሁኔታ ሊካሄድ ችሏል።
ቅርንጫፉ ዓለም አቀፍ የመስማት የተሳናቸው ሳምንት 2010 ዓ.ም. ሐዋሳ ከተማ ውስጥ ለሶስት ቀናት አክብሯል። የመክፈቻው በዓል ኃይሌ ሮዞርት ውስጥ የተካሄደ ሲሆን መስማት የተሳናቸው፣ ሌሎች አካል ጉዳተኞችና አንዳንድ የሕብረተሰቡ አባሎች ተሳትፈዋል። በዓሉ በኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበር ፕሬዚዳንት ባደረጉት ንግግር ተከፍቷል። መስማት የተሳናቸው አባሎች የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ከሚገኝበት አካባቢ ጀምረው እሰከ ኃይሌ ሪዞርት ድረስ የሶስት ኪሎ ሜትር የእግር ጉዞ አድርገዋል። የእግር ጉዞው በተደረገበት ወቅት የከተማው ፖሊስ ተጓዦቹን በማጀብና የትራፊክ ፍሰቱን በመቆጣጠር መልካም ትብብር አድርገዋል። የክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያም ለሥነ-ሥርዓቱ ሽፋን ሰጥቶታል።
የበዓሉ ስፖንሰሮች፡-
- የደቡብ ክልል የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ኤጀንሲ
- ኃይሌ ሪዞርት
- ሰንተራል ሆቴል
- ዓለም አቀፍ እርዳታ አገልግሎት
- ብርሃን ለሕፃናት
- ሠላም አዋሳ
የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበር (ኢመየብማ) እና የሐዋሳ ቅርንጫፍ ከላይ ለተዘረዘሩት ለበዓሉ መሳካት ድጋፍ ላደረጉትና እንዲሁም ለከተማው ፖሊስና ለክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ ልባዊ ምስጋናቸውን እያቀረቡ፣ ለመደፊቱም ትብብራቸው እንደማይለያቸው ያላቸውን ተሰፋ ይገልጻሉ።