ስፖርት
የመስማት የተሳናቸው ስፖርታዊ ተሳትፎ ከኢመየብማ ምሥረታ ጀምሮ የነበረ ነው።
ኢመየብማ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ያለማቋረጥ እንቅስቃሴ ሲያደርግበት የቆየ ነገር ቢኖር የአባሎቹ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ነው። የአባሎች ስፖርታዊ ተሳትፎ ለማገዝ ሲባል የማኅበሩ አባሎች በሙሉ በየወሩ ለአባልነት ከሚከፍሉት መዋጮ በተጨማሪ ገንዘብ ሲያዋጡ ቆይተዋል። ለስፖርት ተብሎ የሚዋጣው ገንዘብ መጠኑ ትንሽ ቢሆንም የማኅበሩ አባሎች ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ለመደገፍ ያላቸውን በጎ ፍቃደኝነት ለማሳዬት ግን በቂ ነው።
የጉዳተኞች ዓመታዊ የስፖርት ውድድሮች
መንግሥታዊው የስፖርት ኮሚሽን ጉዳተኞችን በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ተሳታፊዎች እንዲሆኑ ማድረግ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ጉዳተኞች በራሳቸው ጥረት ተሰባስበው በየዓመቱ የስፖርት ውድድሮች ሲያካሂዱ ቆይተዋል። በነዚህ ውድድሮች ከሐገረ ጥበብ ፋብሪካ፣ ከተዋህዶ ጥበብ የጃንጥላና የባትሪ ድንጋይ ፋብሪካ እና ከኢመየብማ የተውጣጡ ስፖርተኞች ይሳተፉባቸው ነበር። የኢመየብማ አባሎች ወደ አዳማ፣ ድሬዳዋ እና ጅማ ሳይቀር እየሄዱ በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ተሳታፊዎች ሲሆኑ ቆይተዋል።
የእግር ኳስ ጨዋታ በመስማት የተሳናቸው ተወዳጅ ነው።
ከስፖትር ዓይነቶች ሁሉ በይበልጥ በመስማት የተሳናቸው የሚዘወተረው ስፖርት የእግር ኳስ ጨዋታ ነው። በዚህ በኩል መስማት የተሳናቸው በጣም ንቁ ተሳታፊዎች መሆናቸው የተነሳ ላንዳንዶች ስፖርት ማለት የእግር ኳስ ጨዋታ ብቻ ነው። በውድድሮች ብቻ ሳይሆን ለጊዜ ማሳለፍያነት ጭምር እግር ኳስ በጣም የሚወዱት የስፖርት ዓይነት ነው።
ኢመየብማ የራሱ የሆነ የእግር ካስ ማዘውተሪያ ቦታ የሌለው በመሆኑ፡ መስማት የተሳናቸው የእግር ኳስ ተጫዋቾች ከግዮን ሆቴል አጠገብ ይገኝ የነበረ ክፍት ቦታ ይጠቀሙ ነበር። ያ ክፍት ቦታ ሆቴሉ ጠቅልሎ በመያዝ የሆቴሉ አካል እንዲሆን በማድረግ ወደ መናፈሻ ቦታነት (ፓርክ) ሲቀይረው፣ አባሎች አቧሬ አካባቢ ይገኝ ወደ ነበረ ክፍት ቦታ በመሄድ ይጫወቱ ነበር።
ነገር ግን ያ ክፍት ቦታም ለመኖሪያ ቤት ልማት ተወሰደ። ይህ ከሆነ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ መስማት የተሳናቸው የእግር ኳስ ተጨዋቾች የጦር ኃይሎች ሆስፒታል አካባቢ ይገኝ ወደ ነበረ ሜዳ በመሄድ ይጫወቱ ነበር። ከዚያ በኋላ ኢመየብማ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጠይቆ በሳምንታዊ የዕረፍት ቀናት የማኅበሩ አባሎች እንዲጠቀሙ ስለተፈቀደለት ስድስት ኪሎ ግቢ ውስጥ ይገኙ የነበሩት የእግር ኳስና የቮሊቦል ሜዳዎች ለጥቂት ዓመታት ተጠቅመዋል። በአሁኑ ጊዜ ግን አባሎች ጃን ሜዳ በሚገኘው ማዘውተሪያ እየተጠቀሙ ይገኛሉ።
የስፖርት ማዘውተሪያ ቋሚ በሆነ ሁኔታ ባለማግኘታቸው የማኅበሩ ስፖርተኞች ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎች ገጥሞዋቸዋል። ነገር ግን ለስፖርቱ ካላቸው ፀኑ ፍቅር የተነሳ ሁሉንም ችግር ተቋቁመው ሲሳተፉ ቆይተዋል።
አትሌቲክስ
አትሌቲክስም በብዙ አባሎች ይወደዳል። ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ የሯጮች አገር እንደመሆኗ መጠን መስማት የተሳናቸውም የአትሌቲክስ አፍቃሪዎች ናቸው።
የመስማት የተሳናቸው ሴቶች ተሳትፎ
መስማት የተሳናቸው ሴቶች አባሎችም በስፖርት ንቁ ተሳታፊዎች ነበሩ። በቤት ውስጥ ስፖርት ያደርጉት ከነበረው ተሳትፎ በተጨማሪ በሳምንታዊ የቮሊቦል፣ የፈጣን ሩጫና ሶመሶማ ተሳታፊዎች ነበሩ። በዓመታዊ የስፖርት ውድድሮችም በንቃት ይሳተፉ ነበር።
ኢመየብማ በዓመታዊ የስፖርት ውድድሮች ሜዳሊያዎች በማሸነፍ የተሳካላቸው ፈጣን ሴት ሯጮች ነበሩት።
የቤት ውስጥ ጨማታዎች
የቤት ውስጥ ስፖርት ጨዋታዎችም በብዛት ከሚዘወተሩት የስፖርት ዓይነቶች ነበሩ። መስማት የተሳናቸው የጠረጴዛ ቴኒስ፣ ዳርተስ፣ ዳና፣ ቼስ በኢመየብማ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ይጫወቱ ነበር። ሁልጊዜ ሮብ፣ ዓርብ፣ በሳምንታዊ የዕረፍት ቀናትና በሕዝባዊ በዓላት ጊዜ ለመወዳደርና ለመመልከት በመጡ አባሎች ይሞላ ነበር።
አባሎች እርስ በርሳቸው በሚያደርጉዋቸው ውድድሮች ብቻ ሳይወሰኑ፣ በየዓመቱ ይደረጉ በነበሩት ውድድሮች በመሳተፍ ከሌሎች ቡድኖች ጋርም የሚወዳደሩ አባሎች ነበሩን።
ከዚህ ሁሉ ያለማጋነን ለማለት የሚቻለው ኢመየብማ የአቅም ውሱንነት የነበረው ቢሆንም እንኳ ለመስማት የተሳናቸው ስፖርት ዕድገት ብዙ መሥራቱን ነው።