ኢመየብማ
ከዬት ወደ ዬት?
የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበር ከመቋቋሙ በፊት መስማት የተሳናቸው ብዙ ችግሮች ነበሩባቸው። ሕብረተሰቡ መስማት የተሳናቸውን ሰዎች መማር አይችሉም የሚል አተያይ ነበረው። መስማት የተሳነው ሰው በአማርኛ ቋንቋ "ደንቆሮ" ተብሎ ይጠራ ነበር። ይህም ማለት ያልተማረ ወይም ሊማር የማይችል የሚል ትርጉም ነበረው። ለሥራ ስምሪት እና ሌሎች ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ዕድሎችም አልነበሩም። በመንግስት የሚተዳደሩ የዓይነ ሥውራን አዳሪ ትምህርት ቤቶች የነበሩ ቢሆኑም ለመስማት የተሳናቸው ግን በመንግሥት የሚተዳደር ምንም ነገር አልነበረም። በአዲስ አበባ ውስጥ ሁለት፣ ከረን፣ ኤርትራ ውስጥ ደግሞ አንድ የመስማት የተሳናቸው ትምህርት ቤቶች የነበሩ ቢሆኑም፣ እነዚህ ትምህርት ቤቶች ዋና ዓላማቸው ሃይማኖት ማስተማር በሆነ ከውጭ በመጡ ሚስዮኖች ተከፍተው የሚሠሩ ነበሩ።
አንዳንድ ቤተሰቦች መስማት የተሳነው ልጅ መውለድ ከእግዚብሔር እንደመጣ ርግማን ጋር ማገናኘታቸው እንግዳ ነገር አልነበረም። መስማት ለተሳነው ልጅ መውለድ ርግማን ነው የሚለው የሕብረተሰቡ አሉታዊ አመለካከት ለአንዳንድ ቤተሰቦች መስማት የተሳናቸው ሕፃናትን ከሕዝብ እይታ ለመደበቅ በቂ ምክንያት ሆኖ ነበር።
የኢመየብማ ሕልውና እውን የሆነው እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ ነበር። መስማት የተሳናቸው ሰዎች ለመብቶቻቸው ሊከራከሩ የሚችሉበት አንድ ማኅበር ያስፈልግ ነበር።
ንቃተ ሕሊናቸው የዳበረ መስማት የተሳናቸው ሰዎች አንድ ማሕበር እንዲመሠረት ለማድረግ ይንቀሳቅሱ ነበር። በወቅቱ ማህበር ማቋቋም በጣም አደገኛ ሥራ ነበር። ወቅቱ ማንኛውም ዓይነት ማኅበራት መንግሥት ጥርጣሬ የሚያይበት ጊዜ ነበር። መስከረም 3 ቀን 1963 ዓ.ም. መስማት የተሳናቸው እና መስማት የተሳናቸው ወዳጆችን ዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ አጠገብ በሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ግቢ ውስጥ ተሰብስበው ከተነጋገሩ በኋላ ማኅበሩን ለማቋቋም ወሰኑ። (የመሥራች አባሎችን ስም ዝርዘር ለማየት እዚህ ይጫኑ።) ስለሆነም የኢትዮጵያ ማስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበር (ኢመየብማ) ተወለደ። ሰባት ሰዎች ያቀፈ አንድ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ (አምስት መስማት የተሳናቸው ወንዶች፣ አንዲት መስማት የተሳናት ሴት እና አንድ የሚሰሙ የምልክት ቋንቋ የሚያውቁ መስማት የተሳናቸው ወዳጅ) ተመርጠዋል።
የኢመየብማ ቦርድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣኖችን አቅፎ የነበረ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ስድስቱ ሰሚዎች ሲሆኑ አንዱ ግን መስማት የተሳናቸው ነበሩ። እጅግ ብዙ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ያበረከቱ ሲሆኑ፣ ማኅበራት ለማቋቋም አመቺ ባልነበረበት ወቅት ማኅበሩ ከጥርጣሬ ነፃ ሆኖ እንዲንቀሳቀስ መልካም ዕድል ፈጥረውለታል።
ኢመየብማ የወላጆች ኮሚቴ የነበረው ሲሆን፣ ኮሚቴውም ከወላጆች፣ ከቤተሰብ አባላት እና ከመስማት የተሳናቸው ጓደኞች የተውጣጡ ሰባት አባላትን ያቀፈ ነበር።
ሁሉም የዕለት ከዕለት ሥራዎች በሥራ አስፈፃሚው ኮሚቴ ይካሄዱ ነበር። የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ደግሞ ከኮሚቴው አቅም በላይ በሆኑ ጉዳዮች፣ የመንግሥት ፖሊሲ እና ሌሎች ጉዳዮች ከማኅበሩ ቦርድ የተለያዩ መመሪያዎችና ምክር ያገኝ ነበር።
ይህ መዋቅር በመስከረም 1967 መንግሥት ለውጥ እስከ ተካሄደበት ድረስ ሥራ ላይ ቆይቷል። ሆኖም የማኅበሩ የሥራ አመራር ኮሚቴ እስከ ነሐሴ 1969 ድረስ አልተቀየረም ነበር።
የተከናወኑ እንቅስቃሴዎች
በዚህ ጊዜ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ቀደም ሲል እንደ ተገለጸው በሕብረተሰቡ መማር እንደማይችሉ ተደርገው ይታዩ ነበር። ይህ እንደ ነበር የሚያሳይ መስማት የተሳናቸውን ለማመልከት ወይም ለመለየት ጥቅም ላይ ውሎ የነበረው ቃል የሚያስተላልፈው መልዕክት ነው። ቃሉም ስለ የመስማት ኃይል አለመኖር ሳይሆን ስለ መስማት የተሳናቸው ሰዎች አእምሮ ትምህርት የመቀበል ችሎታ እና አቅም እንደሌለው አድርጎ የሚያመለክት ነበር።
ስለዚህ በኢመየብማ የተከናወነው የመጀመሪያው እንቅስቃሴ መስማት የተሳናቸው ምን ምን ተግባራት ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ ጥናት ማድረግ ነበር። መስማት ለተሳናቸው ብዙ የተለያዩ የሥራ እንቅስቃሴዎች ላይ ተሰማርተው ተገኝተዋል። ከዚህም በላይ ጥቂቶቹ የራሳቸው ድርጅቶች ባለቤቶች ነበሩ፤ እንዲሁም መስማት ለሚችሉ ሌሎች ሰዎችን የሥራ ዕድል ሰጥተው ነበር።
በሕብረተሰቡ የተያዘው የተሳሳተ አመለካከት ለመለወጥ እንዲቻል የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በመስማት የተሳናቸው የተሠሩ (የተመረቱ) ምርቶች የሚታይበት ኤግዚቢሽን ለማዘጋጀት ወሰነ። በዚሁም መሠረት ኤግዚቢሽኑ መስከረም 1964 ዓ.ም. የተካሄደ ሲሆን መስማት የተሳናቸው፣ የመስማት የተሳናቸው ወላጆች፣ ወዳጆቻቸውና የተጋበዙ እንግዶች በተገኙበት በንጉሠ ነገሥቱ ተመርቆ ተከፍቷል። ከመክፈቻው ሥነ ሥርዓት በኋላ ኤግዚቢሽኑ በሕዝብ እንዲታይ ለአንድ ሳምንት ክፍት ተደርጎ ቆይቷል።
በኤግዚቢሽኑ ላይ በተለያዩ የሥራ መስኮች የተሰማሩ መስማት የተሳናቸው ተሳትፈዋል። ከነዚህም መካከል የሥነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ የወርቅና ብር አንጠረኞች፣ አናፂዎች፣ የልብስ ስፌት ድርጅት ባለቤቶች እና ልብስ ሰፊዎች፣ የጫማ ፋብሪካ ባለቤት፣ ወዘተ. ነበሩበት።
ዕርዳታ የማግኘት ችግር
መስማት የተሳናቸው የተሰማሩባቸው የሥራ እንቅስቃሴዎች ጥናትን ተከትሎ ማኅበሩ በቆዳ እና በእንጨት ሥራ አነስተኛ የማምረቻ ድርጅቶች ለማቋቋም የሚያስቸሉ ሁለት ፕሮጄክቶች አዘጋጅቶ ነበር። እነዚህ ፕሮጄክቶች መስማት ለተሳናቸው የሥራ ዕድል ለመፍጠርና ሌሎች ተመሳሳይ ሥራዎችን ለማካሄድ እንዲቻል ለማኅበሩ አንዳንድ ገቢዎችን እንዲያስገኙ ታስበው የተዘጋጁ ነበሩ። ነገር ግን በሚያሳዝን ሁኔታ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ፕሮጀክቶቹን ተግባራዊ ማድረግ ሳይቻል ቀርቷል።
ማኅበሩ ምንም ዓይነት አስተማማኝ የገቢ ምንጭ አልነበረውም። ብቸኛው የገቢ ምንጭ የአባልነት መዋጮ ብቻ ነበር። ነገር ግን የአባሎቻችን የአባልነት መዋጮ የመክፈል አቅም እጅግ በጣም ውስን ነበር። ለበርካታ ዓመታት በወር አንድ ብር (ብር 1.00) ሆኖ የቆየ ሲሆን፣ ይህም በጣም አነስተኛ ነበር። ብዙዎቹ አባሎቻችን ተቀጥረው የመሥራት ዕድላቸው ጠባብ ስለነበር የአባልነት መዋጮ የመክፈል አቅማቸው ውሱንነት የአባልነት መዋጮው በዝቅተኛነቱ ለረጂም ጊዜ እንዲቀጥል አስተዋፅኦ አድርጎ ቆይቷል።
ማኅበሩ ለአባሎቹ አገልግሎት ለመስጠት የሚችልበት ቋሚ አድራሻ አልነበረውም። ማኅበሩ እንደተቋቋመ በመጀመሪያ አካባቢ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ውስጥ ይገኝ በነበረው ካፌ ውስጥ ይሰበሰብ ነበር። ከዚያ በመቀጠል ኮሚቴው በሁለት የተለያዩ ቦታዎች ይሰበሰብ ነበር። ከማኅበራችን መሥራቾች አንዱ የሆኑትና እንዲሁም ለማኅበሩ መመሥረት ዋና አነቃቂ እንደ ነበሩ የሚነገርላቸው አቶ ተስፋዬ ባንቲዋሉ፣ የመጀመሪያው የማኅበሩ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ነበሩ። ሙያቸውም የወርቅና የብር አንጣሪነት ነበር። የመሥሪያና የመሸጫ ሱቃቸውም በጣም አመቺ በሆነው የአቡነ ጴጥሮስ አደባባይ በሚገኝበት አካባቢ የነበረ ሲሆን፣ ይህም አካባቢ የብዙ መስማት የተሳናቸው መገናኛ ነበር። በመሆኑም ኮሚቴው የመሰብሰቢያ ቦታ ባስፈለገው ጊዜ ሁሉ የኮሚቴው አባሎች ሱቃቸው ውስጥ እንዲሰበሰቡ እጆቻቸውን ዘርግተው ይቀበሉዋቸው ነበር።
ሁለተኛው ኮሚቴው አዘውትሮ ይሰበሰብበት የነበረበት ቦታ ደግሞ የማኅበሩ አባሎች ወርሃዊ ስብሰባዎች ያደርጉበት ከነበረው ከሠራተኛና ማኅበሪዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አጠገብ ነበር። ይህም ቦታ የመጀመሪያው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ባይሆኑም ቀጥሎ የተመረጠው ኮሚቴ አባል የነበሩት የአቶ ጌታቸው ገብረሕይወት መኖሪያ ቤት ውስጥ ነበር። ኮሚቴው የራሱ ቋሚ ቦታ እስካገኘበት ጊዜ ድረስ አቶ ጌታቸው ቤት ሲሰበሰብ ቆይቷል። በመሆኑም በቋሚ የሥራ ቦታ እና በገንዘብ እጦት የማኅበሩን እንቅስቃሴዎች ለማካሄድ በጣም ፈታኝ ሆኖ ቀይቶ ነበር።
ለአባሎች መደበኛና ቋሚ በሆነ መልክ አገልግሎት መስጠት የተጀመረው የማኅበሩ ቦርድ ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሊቀመንበሩ ወርሃዊ ደመወዝ ከተዋህዶ ጥበብ የጃንጥላ ፋብሪካ እንዲከፈል ማመቻቸት ካደረገ በኋላ ነበር። ፋብሪካው መስማት የተሳናቸውን ጨምሮ አካል ጉዳተኞች ቀጥሮ የሚያሠራ ኩባንያ ነበር። በተጨማሪም በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሥር ይተዳደር ከነበረው ማዕከላዊ የብሬይል ቤተ-መጻሕፍት ይገኝበት ከነበረው ሕንፃ ውስጥ አንድ ክፍል ያለው ጽሕፈት ቤት ለማኅበሩ አገልግሎት እንዲሰጠው ተደርጓል። የታይፒስት ደመወዝ ደግሞ ከማኅበሩ ከቦርድ አባሎች አንዱ በነበሩት በክቡር አቶ ደምሴ አደፍርሰው ይከፈል ነበር። ይህ የተደረገው ማመቻቸት በ1966 ዓ.ም. አብዮቱ ከፈነዳ በኋላ ለጥቂት ዓመታት ቀጥሎ ቀይቷል።
የአብዮቱ በ1966 ዓ.ም. ከመፈንዳቱ ጥቂት ወራት ቀደም ብሎ በማኅበሩ ቦርዱ ሊቀመንበር በኩል ከአዲሰ አበባ ቄራዎች ድርጅት ሁለት የአከአሲዮኖች ድርሻ ለማኅበሩ እንዲሰጥ መፈቀዱን የሚያበስር መልዕክት ተነግሮ ነበር። የሚያሳዝነው ከአብዮቱ ፍንዳታ በኋላ ድርጅቱ በመንገሥት ንብረትነት በመያዙ ስለ ጉዳዩ ዳግመኛ ምንም ነገር ማኅበሩ አልሰማም። በመሆኑም ማኅበሩ ከንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት አንዳችም ነገር አላገኘም።
ማኅበሩ ከመንግሥት አንዳች ዓይነት ነገር ያልደረሰው የማኅበሩ መሪዎች ምንም ዓይነት ጥረት ባለማደረጋቸው ምክንያት አልነበረም። በወቅቱ ያለ ንጉሠ ነገሥቱ ዕውቅናና ይሁንታ ምንም ነገር ሊደረግ አይችልም ነበር። ለኤግዚቢሽኑ መዘጋጀት አንዱ ምክንያት የንጉሠ ነገሥቱን ትኩረት ለማግኘት እንዲቻል በማሰብ ነበር። ሆኖም ግን ያ ምንም አልሠራም። እናም የጃንሆይ 81ኛ የልደት ቀን ሲከበር መስማት የተሳናቸው እፊታቸው ቀርበው መልካም የልደት ቀን ይሁንልዎት ለማለትና ስጦታም ለማበርክት እንዲፈቀድላቸው ማኅበሩ ጠይቋል። ስጦታውም የወርቅና የብር ሠራተኛ በሆኑ የማኅበሩ አባል እንዲሠራ አድርጓል። የተሠራው በብር የተለበጡ ሁለት የዝሆን ጥርሶች ሆኖ ከዝሆን ጥርሶቹ ጫፎች ላይ ደግሞ የንጉሠ ነገሥቱ ዘውድ ምስል እንዲንጠለጠል ተደርጎ አምሮ የተሠራ ነበር። ስለ ሁለቱ የአክሲዮኖች ድርሻ ለማኅበሩ መሰጠት የተነገረው ከዚህ ሥነ-ሥርዓት ከጥቂት ወራት በኋላ ነበር።
ማኀበሩ አንድ ክፍል ያለው ጽሕፈት ቤት ካገኘ በኋላ የቢሮ ዕቃዎች ችግር አጋጥሞት ነበር። ችግሩ ሊፈታ የቻለው [የኢትዮጵያ ወታደራዊ እጓለማውታ ማኅበር ???] አነስተኛ ግን በጣም ጠቃሚ የነበረ ዕርዳታ ስላደረገለት ጠረጴዛ፣ ወንበር እና መደርደሪያ ለመግዛት በመቻሉ ነበር።
ያን ጊዜ እንደ አሁኑ በበጎ አድራጎትና በልማት የሚሳተፉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አልነበሩም። የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በጎ አድራጎት ድርጅት ነበር። ይሁን እንጂ እንቅስቃሴዎቹ ዓይነ ስውራን እና አረጋውያን ላይ ብቻ ነበር የሚያተኩሩት። የድርጅቱ እንቅስቃሴ መስማት የተሳናቸውን አያካትትም ነበር። እንደ ዩኤስ ኤይድ፣ ዳኒዳ፤ ፊኒዳ፤ ሲዳ ያሉ የልማት ድርጅቶችም ነበሩ። ነገር ግን በመንግሥት ተለይተው የተመረጡ ፕሮጀክቶችን ብቻ ይደግፉ ነበር። በተጨማሪም ትኩረቱ በሕፃናት ላይ ያደረገ የኖርዌይ የሕፃናት አድን ድርጅት ይንቀሳቀስ ነበር። ነገር ግን ድርጅቱ መስማት የተሳናቸው ሕፃናት አካትቶ ስለመሥራቱ በእርግጠኝነት ለመናገር አይቻልም። ሁኔታው እንደዚህ ያለ የነበረ በመሆኑ ማኅበሩ ከአባልነት ክፍያ ከሚሰበስበው ትንሽ ገንዘብ በስተቀር ምንም የገንዘብ ምንጭ አልነበረውም።
ስለዚህ ማኅበሩ የሙዚቃ ድግስ በማዘጋጀት የመጀመሪያው የገንዘብ ማሰባሰቢያ እንቅስቃሴውን አከናውኗል። የክብር ዘበኛ፤ የምድር ጦር እና የፖሊስ የሙዚቃ ባንዶች በዝግጅቱ ለመሳተፍ የተስማሙ ሲሆን ዝግጅቱ አንድ ቀን ከሰዓት በኋላ አምባሳደር ትያትር ውስጥ ተካሂዷል። እንደ አለመታደል ሆኖ ለአዳራሽ ኪራይ፣ ለግብር እና ለሌሎች ወጪዎች ከተከፈለ በኋላ የተረፈው ገንዘብ ማንኛውም ፕሮጀክት ለማካሄድ በቂ አልነበረም።
ለመስማት ለተሳናቸው ምንም ዓይነት የትምህርት ፖሊሲ ያልነበረ ቢሆንም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ አንድ መስማት የተሳናቸው ተማሪዎች ተቀብሎ ሲያስተምር የቆየ ትምህርት ቤት ነበር። ይህ ትምህርት ቤት የአዲስ አበባ ሥነ-ጥበብ ጥበብ ትምህርት ቤት ነበር። ትምህርት ቤቱ አዳዲስ ተማሪዎችን ይቀበል የነበረው በክረምት ወቅት የአንድ ወር ሥልጠና በመስጠት እና ተስፋ ሰጪ ችሎታ ያላቸውን በመለየት ነበር። ከዚህም በላይ በዚያ ወቅት የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር የውጭ ዜጋ የነበሩ ሲሆን፤ መስማት የተሳናቸው ሰዎች መማር አይችሉም በሚለው አባባል አስተሳሰባቸው የተበከለ እንዳልነበረ መገመት ይቻላል። ስለዚህ አንዳንድ መስማት የተሳናቸው ሰዎች በዚህ መንገድ ተጠቅመው መመዝገብ ችለዋል። ሌሎች ጥቂት መስማት የተሳናቸው ደግሞ በንጉሠ ነገሥቱ ትዕዛዝ እንዲገቡ የተደረጉ ነበሩ። በመሆኑም ማኅበሩ ከአሥር በላይ አባላቱ የሥነ-ጥበብ ባለሙያዎች ናቸው።
በመስማት የተሳናቸው የሥነ-ጥበብ ባለሙያዎች የተሠሩ የሥነ-ጥበብ ሥራዎች ኤግዚቢሽን በተለያዩ ጊዜያት ቀርበዋል። ኤግዚቢሽን የተካሄዱባቸው ቦታዎች በድሮ አውሮፕላን ማረፊያው አካባቢ ይገኝ የነበረው የአሜሪካ ሕብረተሰብ ትምህርት ቤት፣ ማዘጋጃ ቤት፣ በጎተ ተቋም እና በሌሎች ቦታዎች ውስጥ ነበር። ይሁን እንጂ በጎተ ተቋም የተካሄደው ኤግዚቢሽን ብቻ መስማት ለተሳናቸው ባለሙያዎች የተወሰነ ገቢ እንዳስገኘ ይነገራል። ምክንያቱም ዝግጅቱ በደንብ የተደራጀና የመግዛት አቅም ያላቸው ተሳታፊዎች የታደሙበት ስለ ነበረ ነው። እነኚህ ኤግዚቢሽኖች ከገቢው በተጨማሪ የመስማት የተሳናቸው የሥነ-ጥበብ ባለሙያዎችን ችሎታ እና የጥበብ ሥራዎች እንዲታወቁ አስተዋፅኦ አድርገዋል።
ማኅበሩ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ መስማት ለተሳናቸው ልዩ ፍላጎቶች ላይ አትኩሮት እንዲደረግ ሲቀሰቅስ ቆይቷል። በደርግ ጊዜ ውስጥ ለአጭር ጊዜም ቢሆን የከፍተኛ የደርግ ባለሥልጣኖች እይታ በመሳብ ረገድ የተወሰነ ውጤት አግኝቷል። የሚያሳዝነው ነገር በከፍተኛ አመራሮች ላይ ሁከት የተከተለ ተደጋጋሚ ለውጥ ይደረግ ስለነበር ለማኅበሩ ተሰጥቶ የነበረው ትኩረት ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ አመቺ አልነበረም። ቀደምት መሪዎች ከቦታቸው ከመወገዳቸው በፊት ያስተላለፉዋቸውን ውሳኔዎች በአዲሶቹ እንዲተገበሩ ለማድረግ አስቸጋሪ ነበር።
ቢሆንም ማኅበሩ ስለ መስማት የተሳናቸው ችግሮችና ፍላጎቶች መጠየቁንና ማሳሰቡን ቀጥሎበታል። ከጥቂት ዓመታት በኋላም የማኅበሩ ጥያቄ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ለመድረስ ቻለ። ምክር ቤቱም ከአባሎቹ አንዱ የሆኑትን ክቡር አቶ ወሌ ቼኮል ማኅበሩን እንዲጎበኙና ያለበትን ሁኔታ እንዲመለከቱ በማድረጉ፣ የማኅበሩ ሃላፊዎች ማኅበሩ ያለበትን ሁኔታ እና አባሎች ያሉባቸው አሳሳቢ ችግሮች ለማስረዳት ዕድል አግኝቷል።
ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ማኅበሩን በተመለከተ ውሳኔ ማስተላለፉን ማኅበሩ ለማወቅ ችሏል። ውሳኔውም የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር እና የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በየሥልጣኖቻቸው ሥር ለሚገኙ የማኅበሩ ችግሮች ዕርዳታ እንዲያደርጉለት ነው። ከዚያ በኋላ በምክር ቤቱ የተወሰነውን ተግባራዊ እንዲደረግለት ከበታች ሃላፊዎች ጋር እልህ አስጨራሽ ትግል ቀጥሏል።
ማኅበሩ ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ያጋጠመው ችግር አልነበረም። ምክንያቱም የሚኒስቴሩ መሥሪያ ቤቱ ባለሥልጣኖች ሁልጊዜ ከማኅበሩ ጎን የቆሙ ስለ ነበሩ ነው። በመሆኑም በሥሩ ይገኝ በነበረው "የድኩማን ማቋቋሚያ ድርጅት" ይባል በነበረው ድርጅት በኩል ለማኅበሩ ሠራተኞች ደመወዝ ከመክፈል ጀምሮ በተለያዩ ሁኔታዎች ማኅበሩን በመርዳትና በመደገፍ የድርሻውን ተወጥቷል።
ማኅበሩ አጋጥሞት የነበረው ትልቁ ችግር ከከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር የበታች ባለሥልጣናት ጋር የተያያዘ ነው። የመሬት እና የመኖሪያ ቤት ጉዳዮችን ማካሄድ ምን ጊዜም በችግር የተሞሉ እና ለምግባረ ብልሹ ድርጊቶች የተጋለጡ ናቸው። ችግሩ ከፍተኛ ባለስልጣኖቻቸው ያስተላለፏቸውን ውሳኔዎች ተፈፃሚ በማድረግ በኩል የበታች ባለሥልጣኖች ዳተኛ መሆን፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ፋይሎችን ሆን ብለው ይሁን ወይም በስህተት የተቀመጡበት ቦታ ባለመታወቁ አልተገኙም በማለት የውሳኔው ተፈጻሚነት እንዲጓተት አድርገዋል። ምንም እንኳን ውሳኔው በግልጽ ለማኅበሩ ዕርዳታ እንዲደረግለት፣ ማኅበሩ የጠቆመውን ቤትም ከኪራይ ነፃ ይሰጠው ቢልም፣ የቤት ኪራይ እንዲከፍል በተደጋጋሚ ጊዜ ተጠይቆ ነበር።
በዚህ መንገድ ማኅበሩ የመሰብሰቢያ አዳራሽ እና አሁን ጽሕፈት ቤቱ የሚገኝበትን ቤት ማግኘት ችሏል። ሆኖም ግን የሚኒስሮች ምክር ቤት ያፀደቀው ውሳኔ ቤትን ብቻ ሳይሆን መሬትንም ጭምር ለማኅበሩ እንዲሰጥ የሚል ነበር። ይሁን እንጂ ለረጅም ጊዜ አልተፈታም ነበር። በመጨረሻም የማኅበሩ ጽሕፈት ቤት አቅራቢያ የሚገኝ አንድ ቦታ ተሰጥቶት ነበር። በሚያሳዝን ሁኔታ በገንዘብ እጦት ምክንያት በቦታው ላይ ግንባታ ለማካሄድ አልቻለም ነበር። ስለዚህ የከተማው አስተዳደር መሬቱን መልሶ በመውሰድ ለሌላ አካል አሳልፎ ስለ ሰጠው አሁን መስጊድ ተገንብቶበት ይገኛል።
ማኅበሩ ለትርፍ ያልተቋቋመ የመስማት የተሳናቸው ማኅበር እንደመሆኑና የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎችም በመንግሥት በኩል ለመስማት የተሳናቸው መደረግ ያለባቸውን ተግባሮች የሚደግፉ እንደመሆናቸው መጠን መሬትን ለማልማት የተሠጠው የስድስት ወራት የጊዜ ገደብ በማኅበሩ ላይ ተፈጻሚ መሆን አይገባውም፤ በማለት አቤቱታ በማቅረቡ፣ በከተማው አስተዳደር ሌላ ተተኪ መሬት እንዲሰጠው ተወስኗል። ይሁን እንጂ ተተኪው ቦታ ከከተማው መሃል በጣም ርቆ በሚገኘው ቦሌ ቡልቡላ አካባቢ ነው። መስማት የተሳናቸው በከተማው ውስጥ ተበታትነው የሚገኙ ስለሆኑ በቦሌ ቡልቡላ የሚገኝ ቦታ ለሁሉም መስማት ተሳናቸው ሰዎች በቀላሉ ተደራሽ አይደለም። ከዚህም በላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በርካታ ተማሪዎች በመስማት ተሳናቸው ሕይወት ላይ፣ በምልክት ቋንቋ፣ በመስማት ለተሳናቸው ትምህርት፣ መስማት ለተሳናቸው የሥራ ቅጥር ሁኔታ፣ እና በሌሎች ማህበራዊ፣ ሥነ-ልቦና እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ጥናትና ምርምር ያካሂዳሉ። ማኅበሩ አሁን ያለበት ቦታ ለእነዚህ እንቅስቃሴዎች እንዲሁም መስማት ለተሳናቸው በጣም ተዳራሽ በመሆኑ እጅግ አመቺ ነው። ስለዚህ ለማኅበሩ የሚሰጠው ተተኪ ቦታም እነዚህን ነገሮች ግምት ውስጥ ማስገባት ይገባዋል ብሎ ያምናል። ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ማኅበሩ በቦሌ ቡልቡላ የሚገኘውን ቦታ ለመቀበል ሳይችል ቀርቷል። አሁንም ቢሆን ይበልጥ ምቹ በሆነ ቦታ ላይ ቦታ እንደሚሰጠው በተስፋ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።