መስማት የተሳናቸው አረጋውያን
የኢመየብማ መስማት የተሳናቸው አረጋውያን ክለብ
ባብዛኛዎቹ የበለፀጉት አገሮች ውስጥ አረጋውያን ሲባሉ ዕድማያቸው 65 ዓመት ወይም ከዚያ በላይ የሆናቸው ናቸው። ያ ዕድሜ ባብዛኛው መጦር የሚጀምሩበት የተለመደው ዕድሜ ነው። የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው ከሆነ "... አንድ ሰው አረጋዊ ሆኗል የሚባልበት አጠቃላይ ስምምነት የተደረገበት የዕደሜ ክልል የለም። ቢሆንም ዕድሜው 60 ዓመት ወይም ከዚያ በላይ የሆነው ሰው አረጋዊ እንደሆነ ተደርጎ የማሰብ ስምምነት በተባበሩት መንግሥታት ዘንድ አለ። ኢትዮጵያ ውስጥም ቢሆን ጡሮታ መውጫ ዕድሜ 60 ዓመት እንደ መሆኑ መጠን ዕድማያቸው 60 ዓመት ወይም ከዚያ በላይ የሆናቸውን ሰዎች አረጋውያን እንደሆኑ ይታሰባሉ።
የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበር መስከረም 1963 ዓ.ም ሲመሠረት አብዛኞቹ መሥራች አባሎች ወጣቶች ነበሩ። አሁን ማኅበሩ ከተመሠረተበት ጊዜ ከአራት አሰርተ ዓመታት በኋላ ግን እነዚህ መሥራች አባሎች አብዛኞቹ አረጋውያን ሆነዋል። ሆኖም እስከ ታኅሣሥ 2008 ዓ.ም. ድረስ ለማኅበሩ ህልውና ብዙ መስዋዕት ለከፈሉት ለነዚህ አረጋውያን አባሎቹ ማኅበሩ ምንም ያሰበው ወይም ያደረገው ነገር አልነበረም።
ታኀሣሥ 2008 ዓ.ም. ውስጥ ከማኅበሩ አረጋውያን አባሎች ጥቂቶቹ ተሰባስበው የመስማት የተሳናቸው አረጋውያን ክለብ መሥርተዋል። ለዚህ ክለብ መቋቋም ግፊትና ቅስቀሳ ያደረጉትም በወቅቱ ማኅበሩን በተጠባባቂ ፕሬዚዳንትነት ይመሩ የነበሩት አባል ሲሆኑ፣ መስማት የተሳናቸው አባሎች አስፈላጊው ትኩረት ከማኅበሩ አለማግኘታቸውን አሳሳቢ ሆኖ ስላገኙት ነበር። በአሁኑ ጊዜ የመስማት የተሳናቸው አረጋውያን ክለቡ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ይገኛል። መስማት የተሳናቸው አረጋውያን እየተገናኙ በጋራ ችግሮቻቸው እርስ በርስ እንዲወያዩ ዕድል የፈጠረላቸው ሲሆን ለማኅበሩም ጥሩ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ።
መስማት የተሳናቸው እንግዶችን ተቀብሎ ማስተናገድ
መስማት የተሳናቸው አረጋውያን በመደበኛ ሁኔታ እየተገናኙ ከመወያየታቸውም በላይ በተጨማሪም ከውጭ አገራት የመጡ መስማት የተሳናቸው እንግዶች እየተቀበሉ ሲያስተናግዱ ቆይተዋል፤ ራሳቸውም ተስተናግደዋል። ኔዘርላንድስ ውስጥ Landelijk centrum oudere doven de Gelderhorst (ብሔራዊ የመስማት የተሳናቸው አረጋውያን ማዕከል ?) ከሚባል ለመስማት የተሳናቸው አረጋውያን እንክብካቤ ከሚያደርግ ድርጅት የመጡ የሰሚዎችና የመስማት የተሳናቸው የተካተቱበት ቡድን የካቲት 2008 ዓ.ም. መጥቶ ነበር። ለዚህ ቡድን አባሎች የክለባችን የተወሰኑ አባሎች በየቤቶቻቸው የቡና ሥነ-ሥርዓት መስተንግዶ ያደረጉላቸው ሲሆኑ፣ ቡድኑም ለክለባችን አባሎች የምሳ መስተንግዶ በማድረግ በወቅቱ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ተችሏል። ከዚያ በመቀጠል አራት መስማት የተሳናቸው የተካተቱበት ሌላ ቡድን መጥቶ ለሶስት ወራት የቆየ ሲሆን፣ ከአራቱ መካከል አንዱ አረጋዊ ናቸው። ከዚያ በኋላም ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ መስማት የተሳናቸው የተካተቱበት ቡድን መጥቷል።