የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ እድገት
የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ የጣት ምልክት
ኢትዮጵያ የራሷ ፊደል ያላት ብቸኛዋ አፍሪካዊት አገር ናት። የመስማት የተሳናቸው ትምህርት በሃይማኖት ሚስዮናውያን በኩል ሲገባ (ሲጀመር) በየራሳቸው አገራት የሚገኙ የምልክት ቋንቋዎች ይዘው መጥተዋል። ለመጻፍም የላቲን ፊደል ጥቅም ላይ ውሎ ነበር። የእንግሊዝኛ ቋንቋ ድሮም ሆነ አሁንም ጥቅም ላይ እየዋለ ቢሆንም በኢትዮጵያ ውስጥ አማርኛ የሥራ ቋንቋ እንደ መሆኑ መጠን ተማሪዎችም ቋንቋውን ሲማሩትና በግዕዝ ፊደል ሲጽፉ ነበር።
ነገር ግን መስማት የተሳናቸው ተማሪዎች አማርኛን ከመማር ውጭ ሆነው ነበሩ። አቶ ምናሴ አበራና አቶ ኃይሉ የሱነህ በአንድ ወቅት በአመሃ ደስታ የደናቁርት ትምህርት ቤት (በአሁኑ ጊዜ ማካኒሳ መስማት የተሳናቸው ትምህርት ቤት ተብሎ የሚጠራው) ውስጥ መምህራን ሆነው ይሠሩ ስለነበር የችግሩን አሳሳቢነት በቅርበት ያውቁት ነበር። ስለዚህ፣ አቶ ምናሴ የግዕዝ ሆህያትን በጣት ምልክት ለማሳየት የሚያስችል ዘዴ ለማዘጋጀት በቁ። ዘዴውን በተሟላ ሁኔታ ካዘጋጁ በኋላም የፈጠራ ሥራቸውን ለማኅበሩ (ለኢመየብማ) ስላካፈሉ፣ የማኅበሩ ሊቀመንበር ደግሞ ዘዴው ሶስት አባሎች የሚገኙበት ኮሚቴ በማቋቋም በጥልቀት እንዲታይና እንዲጠና አደረጉ። የኮሚቴው አባላትም አቶ ምናሴ አበራ፣ አቶ ተክለሃይማኖት ደርሶ እና አቶ ኃይሉ የሱነህ ነበሩ። ኮሚቴው በዘዴው ላይ አንዳንድ ተጨማሪ ማሻሻያዎችን ካደረገበት በኋላ የግዕዝ ሆህያትን በጣት ምልክት ለመከወን የሚያስችለው ሥርዓት በማኅበሩ ተቀባይነት አግኝቷል። በመሆኑም የአማርኛ ቃላት ሆህያቱን በምልክት ለማሳየት አስችሏል። እንዲሁም በሌሎች ቋንቋዎች ማለትም ትግርኛ፣ ትግረ እና የመሳሰሉት የግዕዝ ፊደል በመጠቀም የሚጻፉትም በጣት ምልክት ለማሳየት ያስችላል።
በመጀመሪያ የዘጋጀው የ "ሀ" እና "በ" ምልክቶች ተለዋውጠው ነበር። ሆኖም ግን በኋላ ላይ በተደረጉ ክለሳዎች አሁን ባለውን ሁኔታ ኦፊሴላዊ ሆነው እንዲሰራጩ ተደርገዋል።
የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማህበር (ኢመየብማ) በሀገሪቱ ውስጥ ጥቅም ላይ ውሎ የሚገኘው የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ የጣት ምልክት አሠራር ሥርዓት በዓለም መስማት የተሳናቸው ፌዴሬሽን 8ኛው ዓለም አቀፍ ኮንግሬስ (Proceedings of the 8th World Congress of the World Federation of the Deaf) ላይ የቀረቡት ጽሑፎች ስብስብ ላይ ታትሞ የሚገኘው መሆኑን ለሚመለከታቸው ሁሉ ለማስታወቅ ይወዳል።
ከላይ ባለው ዝርዝር ውስጥ አንዳንድ ፊደላት አልተካተቱም። የመጀመሪያው "ቨ" ነው። ማኅበሩ በኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ መዝገበ-ምልክት ውስጥ ከላይ ለተጠቀሰው ፊደል ምልክት እንዲካተት ያደረገ ሲሆን፣ የምልክቱ አደራረግ ደግሞ ለ"በ" በተለሰጠው ዓይነት ሆኖ ነገር ግን ትንሿ ጣት ቀጥ ብላ እንድትቆም በማድረግ ይከወናል። አንዳንድ ቀደምት የማኅበሩ አባሎች፣ በተለይም የጣት ምልክቱን በማዘጋጀት የተሳተፉት አባሎች፣ ለ"በ" የተሰጠውን ምልክት ላይ መሃከለኛውን ጣት በማጠፍ የሚገኘውን ምልክት "ቨ"ን ለማመልከት እየተጠቀሙ ነበር። ይህ ዘዴ በመዝገበ-ምልክቱ ውስጥ ከተካተተው ዘዴ ለመከወን በጣም ቀለል ያለ ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ይህ ምልክት በሆሣዕና መስማት የተሳናቸው ትምህርት ቤት እና በኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ በተዘጋጁ ህትመቶች ላይም ይገኛል።
ሌላው ፊደል "ኧ" ነው። ይህንን ፊደል ለማመልከት ምክንያታዊው ዘዴ "አ"ን ለመከወን ጥቅም ላይ የዋለው ምልክት ላይ ትንሿ ጣት ቀጥ ብላ እንድትቆም በማድረግ መሆን ይገባው ነበር። ነገር ግን ውጤቱ የላቲኑን "Y" ምልክት ስለሚሆን የትኛው ሆሄ ለማመልክት እንደተፈለገ ለማወቅ የሚያስቸግር አሻሚ ሁኔታ ሊፈጥር ስለሚችል ተመራጭ አይደለም። ሌሎቹ ደግሞ በአብዛኛው ዲቃላ ፊደላትና ፍንጽቆች ተብለው የሚታወቁት ሲሆኑ በተለይም ተዘውትረው የሚያጋጥሙ ፍንጽቆች "ሏ"፣ "ሟ"፣ "ሯ"፣ "ሷ"፣ "ሿ"፣ "ቋ"፣ "ኋ"፣ "ኳ"፣ "ጓ" ወዘተ. ናቸው። እያንዳንቸው የሁለት ፊደላት ምልክቶችን በመጠቀም መከወን ይቻላል። ለምሳሌ፣ "ቋ"ን ለማሳየት ከተፈለገ የ"ቁ" እና "ዋ"ን ምልክቶች መጠቀም ነው። ይሁን እንጂ የመስማት የተሳናቸው ማህበረሰብ የምልክቱ ተጠቃሚዎች ቀለል ባለ መንገድ የሚከወንበት ዘዴ ፈጥረዋል። ይህም መሠረታዊውን ምልክት (ለግዕዙ የተሰጠው ምልክት) ተጠቅሞ ወደታች ቀጥሎም ወደ ላይ አቅጣጫ በማዞር መከወን ሲሆን፣ አስተማሪ የፈተና ወረቀት ሲያርም መልስ ትክክል መሆኑን ለማመልከት ወረቀት ላይ ምልክት ሲያደርግ የሚከተለውን አቅጣጫ አየር ላይ ማድረግ ነው። ለምሳሌ የ"ቋ" ምልክት ለመከወን ከተፈለገ የ"ቀ"ን ምልክት ተጠቅሞ አየር ላይ የትክክል ምልክት (✓) ማድረግ ነው።
"ቐ" እና ተከታዮቹ የሚወክሉዋቸው ድምፆች በአማርኛ ቋንቋ ውስጥ አይገኙም። ለዚህ ፊደልም በማኅበሩ የተፈጠረ ምልክት የለም። ይሁን እንጂ ድምፁ በትግሪኛ ቋንቋ በስፋት ይገኛል። ተጠቃሚዎቹ የ"ቀ" ምልክት ላይ ትንሿ ጣት ቀጥ ብላ እንድትቆም በማድረግ የሚገኘውን ምልክት መጠቀም ይችላሉ።
የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ መጽሐፍ
የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ የጣት ምልክት በአጥጋቢ ሁኔታ ካስተዋወቀ በኋላ ማኅበሩ የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ሥርኣት ማዳበርን በተመለከተ መገፋፋት (ማነሳሳት) ጀመረ። እስከዚያ ደረስ መስማት የተሳናቸው ኢትዮጵያውያን ከሰሜን አሜሪካ፣ ከፊንላንድና ከስዊድን እንዲሁም በጥቂቱም ቢሆን አገር በቀል ምልክቶች ሲጠቀሙ ነበር። የአሜሪካ ምልክት ቋንቋ በተለይ ጥቅም ላይ ውሎ የነበረው አዲስ አበባ ውስጥ ሲሆን ከኖርዲክ አገሮች የመጣው የምልክት ቋንቋ ደግሞ በዚያን ጊዜ የኢትዮጵያ አካል በነበረው ኤርትራ ውስጥ ጥቅም ላይ ውሎ ነበር። ኤርትራ የነበሩት አንዳንድ መስማት የተሳናቸው ወደ አዲስ አበባ በመምጣታቸው ምክንያት የኖርዲክ አገሮች ምልክት ቋንቋ አዲስ አበባ ለመግባት ረጂም ጊዜ አላስፈለገውም ነበር።
በቋንቋና በባህል ባለው ጥብቅ ቁርኝት ምክንያት መስማት የተሳናቸው ኢትዮጵያውያን የራሳቸው ምልክት ቋንቋ ማዳበራቸው ጠቃሚነቱ የላቀ ነበር። በውጭ አገሮች የማይገኙና የውጭ አገራት ምልቅት ቋንቋ በመጠቀማችን ምክንያት ምልክቶች ያልተፈጠሩላቸው ብዙ ቃላትና ፅንሰ ሃሳቦች ነበሩን።
የማኅበሩ ጥያቄ ተከትሎም ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከአልፋ መስማት የተሳናቸው ትምህርት ቤት፣ ከመካኒሳ መስማት የተሳናቸው ትምህርት ቤት (ያኔ አመሃ ደስታ የደናቁርት ትምህርት ቤት ተብሎ ይታወቅ የነበረው) እና ከኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበር (ኢመየብማ) የተወከሉ በአባልነት የሚገኙበት ኮሚቴ ተቋቋመ። ይህም የሆነው ታኅሣሥ 7 ቀን 1968 ዓ.ም. ነበር።
በጣም ከባድ ከሆነ ሥራ በኋላ፣ ኮሚቴው 1,009 ምልክቶች አሰባስቦ በማዘጋጀት ነሐሴ 1968 ዓ.ም. ውስጥ ሥራውን አጠናቀቀ። የአርትኦት ተግባሩና ለምልክቶቹ ተገቢውን ሥዕል የማዘጋጀቱ እንዲሁም መጽሐፉን ለሕትመት ብቁ አድርጎ የማዘጋጀቱን፣ የማኅበራችን አባል የሆኑት አቶ ዓለምሰገድ አርኣያ ሥዕሎቹን ሲሠሩ የምልክቶቹን አደራረግ እንዴት እንደሆነ የማሳየቱን ተግባር ጭምር ኃላፊነቱ ለማኅበሩ ተሰጠ። ለማኅበሩ የተሰጡት ተግባሮች በአቶ ኃይሉ የሱነህ የማኅበሩ የመጀመሪያው ሊቀመንበር እና የማኅበሩ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር እጅግ አርኪ በሆነ ሁኔታ ተከናውኗል። ሁለቱ የመስማት የተሳናቸው ትምህርት ቤቶች ለሠዓሊው ለአቶ ዓለምሰገድ አርኣያ በጋራ የድካም ዋጋውን የመክፈል ኃላፊነት ወስደዋል። ትምህርት ሚኒስቴር ደግሞ መጽሐፉን የማሳተም ኃላፊነት ወስዷል።
እንደ አለመታደል ሆኖ የመጽሐፉ ሕትመት አስከ 1971 ድረስ ዘግይቶ ነበር። መጽሐፉ ከታተመ በኋላ ለመስማት የተሳናቸው በነፃ እንዲሠራጭ ኮሚቴው ተስማምቶ ነበር። አሳዛኙ ነገር ይህ ሳይፈጸም ቀርቷል። ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ኃላፊዎች በወቅቱ የተሰጠው ምክንያት ደግሞ ለሰሚዎች ተማሪዎች ከሚዘጋጁት መጻሕፍት ጋር ሲነጻጸር የምልክት ቋንቋው መጽሐፍ ሕትመት ውድ ሆኖ በመገኘቱ ነበር። ለመወደዱ ቀርቦ የነበረው ምክንያት ደግሞ በሁለት ቀለማት፣ ማለትም በጥቁርና ቀይ ቀለሞች፣ በመታተሙ ነበር። በመሆኑም ማኅበሩ ብዙ የደከመበትን መጽሐፍ ሳያገኝ ቀርቷል።
የመጽሐፉ ርእስ "የአማርኛ ምልክት ቋንቋ ለመስማት የተሳናቸው" ይላል። ይህም አባባል "የአማርኛ ምልክት ቋንቋ"" የሚባል ነገር እንዳለ ተደርጎ መታሰብ የለበትም። ይህ መጽሐፍ ከመታተሙ በፊት መስማት የተሳናቸው የአሜሪካ የምልክት ቋንቋ መጻሕፍት ማግኘት ይችሉ ነበር። የምልክቶቹ መግለጫዎች በእንግሊዝኛ ቋንቋ ነበር። በታተመው አዲስ መጽሐፍ ውስጥ ያሉት መግለጫዎች ግን በአማርኛ ቋንቋ ነው። በመጽሐፉ ርእስ ላይ "የአማርኛ" የሚል ቃል መግባቱ የምልክቶቹ መግለጫዎች በእንግሊዝኛ ሳይሆን በአማርኛ መሆናቸውን አትኩሮት ለመሳብና እንግሊዝኛን ለማያውቁ ተዳራሽ መሆኑን ለመጠቆም ተብሎ ነበር።
የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ቋንቋ መዝገበ ምልክት
የ የፊንላንድ መስማት የተሳናቸው ማህበር (FAD) በምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሚገኙት መስማት የተሳናቸው እውነተኛ ወዳጆች አንዱ ነው። በክፍለ አሕጉሩ ለሚገኙት መስማት የተሳናቸው የተለያዩ ሴሚናሮችና ሥልጠናዎች ሲያዘጋጅ ቆይቷል።
ሁለተኛው ምሥራቃዊ እና ደቡባዊ አፍሪካ የምልክት ቋንቋ ሴሚናር በ1983 ዓ.ም. በኢመየብማ አዘጋጅነት ደብረዘይት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የተካሄደ ሲሆን ሴሚናሩ የተዘጋጀው በፊንላንድ መስማት የተሳናቸው ማኅበር የፋይናንስ ድጋፍ ሆኖ፣ የአምስት አፍሪካ አገራት መስማት የተሳናቸው ተሳታፊዎችን ያመጣ ነበር። ኢመየብማ ከፊንላንድ መስማት የተሳናቸው ማኅበር ለወደፊቱ ዕርዳታ ከማግኘቱ አንፃር ሲታይ ኢትዮጵያ በደርግ አገዛዝ ሥር የነበረች በመሆኑ ያ ሴሚናር የአንድ ጊዜና የመጨረሻው ነበር። በዚያን ጊዜ ፊንላንድን ጨምሮ አንዳንድ አገሮች ኢትዮጵያን እንደ ኮሚኒስት አገር አድርገው ይመለከቷት ስለ ነበር ዕርዳታ ከመስጠት የሚከለክል ፖሊሲ ይከተሉ ነበር።
በወቅቱ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ "ሀ" መጽሐፍ ከስርጭት ውጭ ሆኖ ነበር። ከማኅበሩ አባሎች ግልጽ ተደርጎ እንደ ነበረው ከሆነ የመጽሐፉ ተፈላጊነት ከፍተኛ ነበር። ስለዚህ፣ ማኅበሩን ወክለው በመጽሐፉ ዝግጅት ላይ ተሳትፈው ከነበሩት መካከል አንዱና የማኅበሩ የወቅቱ ሊቀመንበር በመተባበር በጉዳዩ ላይ አንድ ነገር ለማድረግ ወሰኑ። በውሳኔያቸውም መጽሐፉን ኤሌክትሮኒክ ቅርጸት ማዘጋጀት ሆኖ ሥራ መሥራት ጀመሩ። በመጀመሪያው "ሀ" መጽሐፍ ላይ ለምልክቶች የተሰጠው መግለጫ በአማርኛ ብቻ ነበር። በኤሌክትሮኒክ ስሪት ላይ ግን መግለጫው ሶስት ተጨማሪ ቋንቋዎች ማለትም ኦሮምኛ፣ ትግሪኛ እና እንግሊዝኛን ለማካተት ወሰኑ።
ጥቂት ገጾች ከተዘጋጁ በኋላ ታንዛኒያ ውስጥ የወደፊት ዕድላችንና መብቶቻችን በሚል መሪ ቃል የኢመየብማ ሊቀመንበር ጭምር የተጋበዙበት በፊንላንድ መስማት የተሳናቸው ማኅበር የተዘጋጀ ሴሚናር ነበር። ሊቀመንበሩ የተዘጋጁትን ምልክቶች ይዘው በመሄድ ለዶክተር ሊዛ ኮፒኔን በማሳየት የዕርዳታ ትብብር ጠየቁ። በወቅቱ የደርግ ሥርዓት በኢሕአዴግ መንግሥት ከተተካ ቆይቶ ስለ ነበር ምዕራባውያን ከኢትዮጵያ ጋር እንዳይተባበሩ የሚያግድ ምንም ምክንያት አልነበራቸውም። ስለዚህ ኢመየብማ በጣም ዕድለኛ ነበር ምክንያቱም FAD የዕርዳታ ጥያቄውን በመቀበሉ ነው።
በENAD እና FAD መካከል ውጤታማ የሆነ የትብብር ሥራ ተጀመረ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የፊንላንድ መስማት የተሳናቸው ማኅበር የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋን የማበልጸግ ድርጊትን ጨምሮ የኢመየብማ የተለያዩ ተግባራት በንቃት ሲረዳ በመቆየቱ የማኅበሩና የአባሎቹ ባለውለታ ነው።
የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ማህበር (ኢመየብማ) የኢትዮጵያን የምልክት ቋንቋ መዝገበ ምልክትን ለሕትመት አብቅቷል። መዝገበ ምልክቱ ለሕትመት የበቃው የፊንላንድ መስማት የተሳናቸው ማኅበር ከኢመየብማ ጋር ባደረገው መተባበርና ባደረገለት የገንዘብ ዕርዳታ ምርምርና ጥናቶችን ለማከናወን፣ ምልክቶችን ወደ መስክ በመሄድ ለመሰብሰብ፣ ለማቀነባበር እና ለሕትመት ለማዘጋጀት በመቻሉ ነው።