አቶ በላይ ተክሉ የዓለም መ.የ. ሳምንት 1992 ሲከበር ኢመየብማን ረዱ።
ሰኔ 17 ቀን 2009 - የኢመየብማ ባልደረባ
የ1992 ዓለም አቀፍ የመስማት የተሳናቸው ሳምንት ነፍሰሄር አቶ በላይ ተክሉ ባደረጉት ዕርዳታ በደመቀ ሁኔታ ተክብሮ ውሏል። አቶ በላይ ተክሉ ብዙ የሥራ እንቅስቃሴ በሚታይበት መርካቶ በተለይም ቅዱስ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን አካባቢ በኬኮችና ጣፋጭ ምግቦች ንግድ በጣም የታወቁ ነበሩ።
የአቶ በላይ ተክሉ እርዳታ ልዩ የሚያደርገው ለማኅበራችን የገንዘብ ድጋፍ ከማድረጋቸውም በላይ መስማት የተሳናቸው አባሎቻችን የጋብቻ ሥነ-ሥርዓታቸውን ሲፈጽሙ የጋብቻ ኬክ በነፃ እንዲወስዱ መፍቀዳቸው ማስታወቃቸውን ነበር። በዚህ በጎ ችሮታ መሠረት አንዳንድ አባሎቻችን ተጠቃሚዎች ሆነዋል። እርዳታውን ለማግኘት ከማኅበራችን ጋብቻቸውን የሚያከብሩ መሆናቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ይዘው መሄድ በቂያቸው ነበር።
አቶ በላይ ተክሉ የማኅበራችንን የስብሰባ አዳራሽ ስብሰባና ትርኢት በሚደረግበት ጊዜ አባሎች እይታ ሳይከለል ለመከታተል እንዲችሉ መድርኩ ክፍ ብሎ እንዲሠራ ለማድረግ ሃሳብ ነበራቸው። በጣም የሚያሳዝነው ግን ሃሳባቸውን ተግባራሚ ከማድረጋቸው በፊት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
አቶ በላይ ተክሉ በሞት ቢለዩም ቤተሰባቸው የጋብቻ ኬክ ለመስማት የተሳናቸው ማበርከቱን ቀጥለውበታል። ማኅበራችን ዓለም አቀፍ የመስማት የተሳናቸው ሳምንት በሚያከብርበት ጊዜም ደረቅ ኬኮች እና የመሳሰሉትን በነፃ ለማኅበራችን ሲያበረክቱ ቆይተዋል። ይህ በጎ ተግባራቸው ለወደፊቱም እንደሚቀጥል ተስፋችን ነው።