አካሌ፣ መብቶቼና የመስማት ስነቴ፡- በአቻ ለአቻ ትምህርት መስማት የተሳናቸው ሴቶችን ማብቃት
ጥቅምት 12 ቀን 2014 - የኢመየብማ ባልደረባ
የኢትዮጵያ መስማት የተሳናች ብሔራዊ ማኅበር በሴቶች አቅም ግንባታ ላይ ያተኮር “አካሌ፣ መብቶቼና የመስማት ስነቴ” ፕሮጄክት ዛሬ ጥቅምት 12 ቀን 2014 ዓ.ም. የአውስትራሊያ ኢምባሲ ተወካዮች በተገኙበት ይፋ አደረገ፡፡
ፕሮጄክቱ ከአውስትራሊያ ኢምባሲ ‘ስሞል ግራንትስ ፕሮግራም’ ማለትም ‘አነስተኛ ድጋፍ ፕሮግራም’ በተገኘ 670,000.00 ብር የሚተገበር ሲሆን ለስድስት ወራት ይቆያል። የፕሮጄክቱ ዋንኛ ዓላማ መስማት የተሳናቸው ሴቶች በራሳቸው ላይ ያላቸውን ሁለንተናዊ መብቶች ተገንዝበው ራሳቸውን ከማንኛውም ዓይነት ጾታዊ ጥቃት የመከላል አቅማቸውን መገንባት ነው። በፕሮጄክቱ ቆይታ በአቻ ለአቻ ትምህርት ቢያንስ የ750 መስማት የተሰናቸው ሴቶችን አቅም ለመገንባት ይሰራለ። ጎን ለጎንም ለ30ሺ ዜጎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ይሠራል። በፕሮጄክቱ ትግበራ ሂደት ላይም በሁሉም ማኅበሩ ቅርንጫፎች ባለፉት አራት ዓመታት የተዳከመውን የማኅበሩን የሴቶች ዘርፍ በአዲስ መልክ የማቋቋምና የማጠናከር ሥራዎችን በማከናወን የመስማት የተሳናቸውን ሴቶች ሁለንተናዊ ችግሮች ለመፍታት ጥረት ይደረጋል።